2017 ሜይ 23, ማክሰኞ

ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር በመሆን ተመረጡ።

ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር በመሆን ተመረጡ።
ዛሬ በስዊዘርላንድ፣ ጄኔቫ በተካሄደው ምርጫ ኢትዮጵያ እጩ አደርጋ ያቀረበቻቸው ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የአብላጫ አገራትን ድምፅ በማግኘት ተመርጠዋል።
በምርጫው ድምፃቸውን ከሰጡት አገራት መካከል 133 አገራት ድምፃቸውን ለዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ሰጥተዋል።
ምርጫው የተካሄደው ትናንት በተጀመረው የአለም ጤና ድርጅት 70ኛ የዓለም የጤና ጉባዔ ላይ ነው።
የድርጅቱን ዋና ዳይሬክተር ለመምረጥ በሶስት ዙር ምርጫ የተካሄደ ሲሆን፥ በመጀመሪያ ዙር ላይ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም 95 ድምፅ፣ ኢንግሊዛዊው እጩ ዶክተር ዴቪድ ናባሮ 52 እና ፓኪስታናዊቷ ዶክተር ሳኒያ ኒሺታር 38 ድምፅ አገኝተዋል።
66 በመቶ ድመፅ ያገኘ ተወዳዳሪ ባለመኖሩም በድርጅቱ የምርጫ ህግ መሰረት ፓኪስታናዊቷ ዶክተር ሳኒያ ኒሺታር ከውድድሩ ወጥተው ከዶክተር ቴድሮስ እና ዶክተር ናባሮ መካከል አንዱን ለመምረጥ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዙር ድምፅ ተሰጥቷል።
በዚህም ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በሶስተኛው ዙር 133 ድምፅ በማግኘት ያሸነፉ ሲሆን፥ ዶክተር ዴቪድ ናባሮ 50 ድምፅ አግኝተዋል።
ዶክተር ዴቪድ ናባሮም ዶክተር ቴድሮስን እንኳን ደስ ያልዎት ያሉ ሲሆን፥ ሁሉም ወገን በአንድነት ከጎናቸው እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።
ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ዶክተር ቴድሮስ ለጉባኤው ባቀረቡት ንግግር ዛሬ በዓለም ለሰው ልጅ ጤና ፈተና ከሆኑት ኢቦላ ጀምሮ እስከ ዘመን አመጣሹ ውፍረት ድረስ ያላቸውን መፍትሄ አስቀምጠዋል።
የዓለም ጤና ድርጀትን ጊዜው የሚፈልገው ዓለም አቀፋዊ ተቋም እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።
ፈታኝ የጤና ጥበቃ ስራ ካለባት አገር የወጡ እንደመሆናቸውም ወደ ድርጅቱ አዲስ አተያይ ይዘው እንደሚመጡ ነው ያስረዱት።
ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በስራቸው የሰው ልጅን እንደሚያስቀድሙ፣ የጤና ጉዳይ የዓለም ዋነኛ አጀንዳ እንዲሆንና ሀገራት በጤናው ዘርፍ ውጤት የሚያስገኝ ስራ እንዲያከናውኑ ለማድረግ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
እንዲሁም የዓለም የጤና ድርጅትን በተሻለ መልኩ ውጤታማ፣ ግልጽ እና ተጠያቂነት የሰፈነበት ተቋም ለማድረግ እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች የጤና አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበትን ዓለም አቀፍ የጤና አገልግሎት ሽፋን እንዲኖር እንደሚያደርጉም አብራርተዋል።
የጤና ደህንነትን በተመለከተም የመንግስት ባለስልጣናት እና የማህበረሰብ አስተዳደሮችን በሽታን ቀድሞ በመለየት፣ በመከላከል እና አስቸኳይ ስራ የሚያስፈልጋቸው የጤና ጉዳዮች ላይ አቅማቸውን የማጠናከር ስራ ላይ ትኩረት እንደሚሰጡም አስታውቀዋል።
የሴቶች፣ የህጻናት እና የወጣቶች የጤና ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት እንዲያገኝ እንዲሁም የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ በጤና ላይ በሚያመጣው ጉዳት እና ለውጥ ላይ ከሀገራትና መንግስታት ጋር እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
ዶክተር ቴድሮስ በእናቶችና ሕጻናት ሞት ቅነሳ፣ የወባና የልጅነት ልምሻ በሽታዎችን ከሃገሪቷ ለመቀነስ ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተደማጭነትን አግኝተዋል።
በዚህ ምክንያትም የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል።
ዶክተር ቴድሮስ በዚህ ምርጫ አሸናፊ ከሆኑ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ እንዲሁም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አስቸጋሪ የሆኑትን የዓለም ጤና ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የመጀመሪያው አፍሪካዊ የዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ሆነዋል።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ